የጋራ ዉል ስምምነት
ይህ ዉል ስምምነት የአባልነት ደንብና ሁኔታዎችን የሚደነግግ ሲሆን አባል መሆን በሚፈልጉት በእርስዎ ( ከዚህ በኋላ አባል ፣አባሉ፣ እቁብተኛ ተብለዉ በሚጠሩ) እና በአትራፊ ሶልዩሽን ፋይናንስ እና ሀዉሲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ (ከዚህ በኋላ ድርጅቱ ተብሎ በሚጠራ) መካከል በዛሬዉ ዕለት ተፈጽሟል ።
አንቀፅ 1
የዉሉ አላማ
አትራፊ ሶሉሺን ፋይናንስ እና ሀዉሲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት የመኪና እቁብ ፕሮግራም የጀመረ ሲሆን ይህን ዉል የሚዋዋል አባል ከዚህ በታች ባሉት አንቀጾች ያሉትን ግዴታዎች ከተወጣ E-star changan ወይንም ተመጣጣኝ እና ተመሳሳይ መኪናን በዓመት 4 /አራት/ ጊዜ በዲጂታል መንገድ በሚወጣ እጣ አማካኝነት ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በጊዜ ሂደት በ 3 /ሶስት/ ዓመት ውስጥ ሁሉም ተዋዋይ የመኪና ባለቤት እንዲሆኑ የማስተባበርና የውክልና ስራ የሚሰራ በመሆኑ አትራፊ ሶሉሽን እና ሃውሲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ የማገናኘት እና የማቀዳጀት ተግባሩን በማከናወን መኪና ፈላጊው የተመዘገበበትን የመኪና አይነት መሰረት በማድረግ ያቀረበውን መኪና ከሌሎች ተመሳሳይ መኪና ፈላጊዎች ጋር በዕጣ አወዳድሮ በስማቸው በማስመዝገብ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል፤ ከመኪና ፈላጊው ጋር በፈቃደኝነት የተደረገ ውል ነው፡፡
አንቀፅ 2
የድርጅቱ መብትና ግዴታ
2.1 ድርጅቱ መኪና ፈላጊ የሆኑ አባላቱን በአሁኑ ዋጋ ግምቱ 2,200,000 ( ሁለት ሚሊየን ሁለት መቶ ሺ) የሆነን ኤሌክትሪክ መኪና ለወደፊት የመኪናዉ ዋጋ ቢጨምር በንዑስ አንቀጽ 3.5 መሰረት አባሉ ሊጨምር ተስማምቶ ፤ እጣ ሲወጣላቸዉ እና በዚህ ዉል ላይ ያሉት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ እጣ ለወጣለት ሰዉ በስሙ መኪና ይገዛል።
2.2 ድርጅቱ በዉሉ መሰረት በተከታታይ መዋጮዋቸዉን ለሚከፍሉ አባላቱ በስነ ስረዓት እየተከታተለ እጣ ዉስጥ እንዲገቡ ያደርጋል በተጨማሪ የእጣ አወጣጥ ሂደቱን ያስፈጽማል ።እጣ የሚወጣትን ወር እና ቀን ይወስናል፡፡
2.3 ድርጅቱ የአባላቱን መዋጮ በመጠቀም ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከግለሰብ ፣ ከድርጅት ፣ ከአበዳሪ ተቋማት በመበደር ግዴታቸዉን ለተወጡ አባላት እጣ እንዲደርሳቸዉ ያረጋል ።
2.4 አባሉ ቀሪ ክፍያዎችን እና እዳዎችን ከፍሎ እስኪጨርስ ድርጅቱ ሊብሬውን (የመኪናው ባለቤትነት ደብተሩ) በአንደኛ ደረጃነት ዋስትናነት ይዞ እንዲቆይ ተስማምቷል። ይህንን ስምምነት ድርጅቱ ለአበዳሪ ተቋማት ለመንገድ ትራንስፖርት.እና ተመሳሳይ ተቋማት ወይም ለሚመለከታቸዉ አካል ዉሉን መሰረት አድርጎ ማሳወቅ ይችላል።
2.5 አባሉ የሚጠበቅበትን መዋጮ መክፈል ካልቻለ እና ተመላሽ ከጠየቀ ድርጅቱ መዋጮውን ተመላሽ የሚያረገዉ ለሁሉም አባላት መኪና ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ብቻ ነዉ ሆኖም መኪና ወስደዉ እዳቸዉን ያልከፈሉ አባላት ያለባቸዉን ክፍያ በአግባቡ ካልከፈሉ ስልጣን ባለዉ አካል ከሶ ብሩ እንዲመለስ ያረጋል እንጂ ከራሱ ተመላሽ ክፍያ ለአባላት አይፈጽምም፡፡
2.6 አባሉ ድርጅቱ መኪና እንዲገዛለት ፣ ተመጣጣኝ ዋስትና ካላቀረበ እንዲያስተዳድርለት እና እንዲያከራይለት እንዲሁም በዚህ ዉል የተጠቀሱ አገልግሎት እና የኮሚሽን ክፍያዎች በአባሉ በኩል ተከፋይ ካልሆኑ ከድርሻዉ ተቀናሽ ሆነዉ ቀሪዉ እዳዉን ማካካሻ ተከፋይ እንዲሆን ለድርጅቱ ሙሉ መብት ሰጥቷል ።
2.7 ድርጅቱ ከአንድ ወር ያነሰ መኪናው በብልሽትም ሆነ በሌላ በማህበራዊና ፓለቲካዊ ችግሮች ስራ ላይ ካልዋለ አባሉን ሳያሳውቅ ሊቆይ ይችላል ከአንድ ወር በላይ ከሆነ አባሉን በስልክ፤ በደብዳቤ፤ በቴክስት፤ ወይም ድርጅቱ ቦርድ ላይ በመለጠፍ ከተጠቀሱት በሁሉም ወይም በአንዱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም መኪናዉ ስራ ባልሰራበት ጊዜ ለሚያጣዉ ገቢና ኪሳራ ድርጀቱ ተጠያቂ አይሆንም ።
2.8 በዚህ ስምምነት ዉስጥ ያልተካተቱ ጉዳዮች በአጠቃላይ ባሉ በእቁብ ህጎች መሰረት ይታያሉ፡፡
2.9 አባሉ መኪና ሲደርሰዉ ድርጅቱ የሚያምንበት ከተገዛዉ መኪና ዉጪ ሌላ ማስያዣ ካላቀረበ ድርጅቱ መኪናዉን እያስተዳደረ በየወሩ በዚህ ዉል ስምምነት መሰረት እና መኪናዉን በስሙ ሲያዞር በሚደረግ ስምምነት መሰረት ብቻ ተፈጻሚ ያረጋል፡፡ ድርጅቱ አባሉ መኪና ደርሶት ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ግዴታ መወጣት ካልቻለ እና ድርጅቱ እንዲያከራይለት ጠይቆ ድርጅቱ የሚከራየዉ ሰዉ ካጣ አባሉ እጣዉ እንዳልደረሰዉ ተቆጥሮ ድርጅቱ በእጣ መስፈርቱን ለሚያሟላ ሌላ አባል መኪናዉን የማስተላለፍ ሙሉ መብት አለዉ።
2.10 ድርጅቱ እጣ ለወጣላቸው አባላት መኪና በሚያስተላልፍበት ወቅት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በሚኖረው ስምምነት መሰረት ተሸከርካሪዎቹን ለእድለኛው የፋይናንስ ተቋማቱ በቀጥታ እንዲያስረክቡ ሊደርግ ይችላል፡፡
2.11 ድርጅቱ መኪናዉን በተመለከተ ለሚያወጣቸዉ የታወቁ ወጪዎች አባሉን የመጠየቅ ሙሉ መብት አለዉ፡፡
አንቀጽ 3
የአባሉ መብትና ግዴታ
3.1 አባሉ የመኪናው እጣ ከደረሰው በኋላ የሚከፍለውን ወርሃዊ መዋጮ ድርጅቱ በሚያቀርበው የአከፋፈል ስረዓት መሰረት ለመክፍል ተስማምቷል።
3.2 አባሉ መኪናው በደረሰው ጊዜ መኪናውን ለመቀበል አስተማማኝ ሌላ ዋስትና ማምጣት ካልቻለ ድርጅቱ በየወሩ መኪናውን እያከራየለት ገቢዉን ወደ ቁጠባው እንዲያደርግለት ተስማምቷል።
3.3 አባሉ የመኪናው እጣ በደረሰው ጊዜ በአንቀፅ 4.1 በፊደል መ ያለዉን ክፍያ ቀድሞ ለመክፈል የግዴታ ዉል ገብቷል እንዲሁም አባሉ ከመኪናው ግዢ በተጨማሪ ያሉ ወጪዎችን ማለትም በስም ማዞሪያ፣ መንገድ ትራንስፖርት ለሚያስፈልጉ ወጪዎች፣ ግዢዉን ላገናኘው ደላላ፣ ለውልና ማስረጃ ዉል መፃፃፊያ ፣ ለኢንሹራንስ፣ ለሰርቪስ፣ ለጋራጅ፣ ለ GPS፣ ለጉዳይ አስፈፃሚ ፤ ለግብር በአጠቃላይ መኪናውን አስመልክቶ እዳውን ጨርሶ በእጁ እስኪገባ ድረስ ያሉትን ወጪዎች ለመክፈል ተስማምቷል።
3.4 አባሉ ለሚቆጥበው ቁጠባ ወይም ተቀማጭ ምንም ዓይነት ወለድ ላለመቀበል የተስማማ ሲሆን እጣዉ በደረሰው ጊዜ ከመኪናው ውጪ ጥሬ ገንዘብ መቀበል አይችልም ። አባሉ እጣ ከደረሰው አባል ውጪ በሌላ ሰው ስም መኪናው እንዳይገዛ ተስማምቷል፤ በተጨማሪ ከእጣ ስነስርአት ውጪ በሽያጭ መልክ እንዲስተናገድ ላለመጠየቅ ተስማምቷል፡፡
3.5 አባሉ በጊዜ ሂደት ውስጥ ከዋጋ ንረት እና እንደ ሀገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲ ለሚደርሱ ተለዋዋጭ ነገሮች ቁጠባውን ድርጅቱ በሚያቀርበዉ ሃሳብ መሰረት ለማስተካከል ተስማምቷል ።
3.6 አባሉ የእቁብ አባላት በሙሉ መኪና ደርሷቸው እስከሚጨርሱ ድረስ በመሀል ላይ ያዋጣውን ገንዘብ ተመላሽ ላይጠይቅ ተስማምቷል፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ተመላሽ ጥያቄ ካቀረበ ለመንግስት 5,000 (አምስት ሺህ) ብር እና ለድርጅቱ 50,000 (አምሳ ሺህ) ብር ቅጣት ተቀጥቶ ዉሉ የጸና ይሆናል፡፡
3.7 አባሉ እጣ በደረሰው ጊዜ ለመኪና መግዣ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ማለትም ማንነቱን የሚገልፅ ዲጅታል መታወቂያ እና ከመንግስት ከእዳ ነፃ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ለማቅረብ ተስማምቷል ።
3.8 አባሉ ድርጅቱን እቁቡን ከፍሎ እስኪ ጨርስ ድረስ ተመጣጣኝ ዋስትና ማቅረብ ካልቻለ ድርጅቱ መኪናውን እንዲያስተዳድርለት፣ እንዲያከራይለት፣ እንዲቆጣጠርለት፣ አስፈላጊ የመንግስት እና ተመሳሳይ መስሪያ ቤቶች ላይ እሱን እንዲወክል ተስማምቷል፤ በተጨማሪም ድርጅቱ እነዚህን ጉዳዮች እና በዚህ ዉል የተሰጡትን ስራዎች ለማስፈጸም እንዲረዳዉ ህጋዊ የዉክልና ስልጣን ይሰጣል፤ እንዲሁም አባሉ ድርጅቱ በስሙ መኪና መግዛት እንዲችል የተገዛለትን መኪናም በአንቀፅ 2.6 መሰረት እንዲያስተዳድር እና እንዲያከራይ የኪራይም ገንዘብንም እንዲቀበል ፣ ለተገዛለት ክፍያ እንዲያዉለዉ ፣ ለድርጀቱ የሚከፈሉ አገልግሎት ክፍያ እና ኮሚሽን ክፍያ እንዲፈጽም እንዲሁም ከማንኛዉም ባንክ ፣ አበዳሪ ተቋማት እና ግለሰብ ሊበደር እና ሊያበድር እንዲችል የተስማማ ሲሆን ለዚህ አፈጻጸም እንዲረዳዉ ህጋዊ ዉክልና ለመስጠት ግዴታ ገብቷል፡፡
3.9 አባሉ ድርጅቱ መኪናውን በየወሩ ከ 30,000 (ሰላሳ ሺህ) ብር ጀምሮ እንዲያከራይለት ተስማምቷል ይህም እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ሀገሪቷ ኢኮኖሚ እና የስራ ሁኔታ 50 በመቶ ድረስ የገቢ ቅናሽ ቢታይ የተሰራዉን ገቢ ለመቀበል ተስማምቷል።
3.10 አባሉ በየዓመቱ ለሚወስደዉ መኪና ሙሉ ኢንሹራንስ ሊገባ የዉዴታ ግዴታ ገብቷል በተጨማሪም አባሉ ኢንሹራንስ ሊሸፍናቸዉ ለማይችሉ ነገሮች በመኪናው ላይ ጉዳት ቢያደርሱ አባሉ ራሱ ወጪዎችን ሊሸፍን ተስማምቷል።
3.11 አባሉ በአንቀጽ 4.1 ያለዉ ክፍያ እና በየወሩ የሚከፍላቸዉ የአገልግሎት ክፍያዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ መኪና ሲገዛለት በአንቀፅ 4.1 በፊደል ሸ መሰረት ለድርጅቱ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ ድርጅቱ ባወጣው የአከፋፈል ስርዓት መሰረት ለመክፈል ተስማምቷል።
3.12 አባሉ መኪናዉን ሲረከብ እና በመሃል ቢሸጥ ለድርጅቱ 2 በመቶ ኮሚሽን ለመክፈል ተስማምቷል።
3.13 አባሉ በአንቀፅ 4.1 ከፊደል ሀ እስከ ሸ ያሉትን ክፍያዎች አሟልቶ የመኪና እጣ ከደረሰዉ በኋላ ከ 60 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ድርጅቱ ባዘጋጀለት የአከፋፈል ስርዓት ክፍያ የመፈጸም ፣ተገቢዉን የመንግስት ግብር እና መኪናዉ በስሙ እንዲሆን አስፈላጊ ቅድመ ክፍያዎችን መፈጸም አለበት ። ነገር ግን ተገቢዉን ክፍያ ካልከፈለ እጣዉ እንዳልደረሰዉ ተቆጥሮ በቀጣይ እጣ ዉስጥ ይካተታል።
3.14 አባሉ የሚጠበቅበትን ወርሃዊ መዋጮ እና ድጎማ ወር በገባ በ 5 ቀን ዉስጥ የመክፈል ግዴታ አለበት፤ በተጠቀሰዉ ጊዜ ካልከፈለ ዋናዉ ሂሳብ ላይ የማይታሰብ ያልተከፈለዉን ብር ተጨማሪ 10 በመቶ እንዲከፈል ይደረጋል።
3.15 አባሉ እጣ ከመዉጣቱ በፊት የእጣ መብቱን ለሌላ ሰዉ ማስተላለፍ አይችልም። እጣ ከወጣለት በኋላ 80 በመቶ የመኪና ዋጋዉን ከሸፈነ በኋላ እና በዚህ ዉል ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ መሸጥ ይችላል፡፡
3.16 አባሉ ለድርጅቱ የሰጠዉን የዉክልና ስልጣን እዳዉን እና የሚጠበቅበትን ክፍያ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ማቋረጥ አይችልም ። መኪናዉንም ድርጀቱ ካልፈቀደለት በስተቀር ለሌላ ሶስተኛ ወገን በማንኛዉም ሁኔታ ማስተላለፍ ፣ ማስያዝ ወዘተ... አይችልም።
3.17 አባሉ መኪናዉ ከደረሰዉ በኋላ እራሱ መንዳት ቢፈልግ አንቅጽ 3.2 ተፈጻሚ ማድረግ ይጠበቅበታል ። እንዲሁም ማስያዥያዉን አምጥቶ መኪናዉን ከወሰደ በኋላ በአንቅፅ 4.1 በፊደል መ ፣ ሠ ፣ ረ ፣ ያለበትን መዋጮ እና ለድርጅቱ በአንቅፅ 4.1 በፊደል ሠ እና ሸ ያለዉን ወራዊ እና የአንድ ጊዜ የአገልግሎት ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለበት ። በተጨማሪም አባሉ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ እና ድርጅቱ የሜትር ታክሲ መተግበሪያ ተጠቃሚ ከሆነ ቅድሚያ የማስተናገድ ግዴታ አለበት።
3.18 አባሉ መኪና በስሙ ከተገዛለት በኋላ አብሮ በተዋጣ በሌሎች አባላት ብር መኪና በመገዛቱ መጨረሻ አካባቢ የሚደርሳቸዉ ሰዎች የመኪና መግዢያ ዋጋ ላይ ጭማሪ ቢያሳይ ጭማሪዉን ብር ጨምሮ ሊከፍል የዉዴታ ግዴታ ዉል ገብቷል አከፋፈሉም ድርጀቱ ባስቀመጠለት አከፋፈል ይሆናል። በተጨማሪም ሁሉም አባል እጣ በደረሰዉ ጊዜ ድርጅቱ ባስቀመጠዉ የመኪና ዋጋ ለመስተናገድ ስምምነት ገብቷል።
3.19 አባሉ ከተመዘገበ እና አባል ከሆነ በኋላ በድርጅቱ አሰራር ላይ ያልተገባ የስም ማጥፋት ቢፈጽም በሚደርሰዉ ጉዳት በፍትሐብሔር እና በወንጀል ተጠያቂ ሆኖ በተጨማሪም በዚህ ውል አንቀፅ 3.6 በተገለጸዉ መሰረት የሚያስከትለዉን ቅጣት አባሉ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።
3.20 አባሉ ከ 18 ዓመት በታች ለሆነ ሰዉ በሞግዚትነት መመዝገብ ይችላል በተጨማሪም በዚህ ዉል ላይ ያሉት አስገዳጅ ዉሎች እንደተጠበቁ ሆነዉ መኪና በደረሰዉ ጊዜ በሌሎች ዉሎች የሚታይ ይሆናል።
3.21 አባሉ ድርጅቱ ብቸኛ የመኪና አቅራቢ እንዲሆን ተስማምቷል፡፡
3.22 ድርጅቱ በማንኛዉም ጊዜ የተከፈሉ ክፍያዎችን ማረጋገጫ በፈለገ ጊዜ አባሉ የማቅረብ ግዴታ አለበት።
3.23 አባሉ የድርጅቱን ዌብ ሳይት መተግበሪያዎችን ሲጠቀም ቲንን ጨምሮ በድርጅቱ የሚላኩ ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን በሚስጥር መያዝና ይህን ባለማረግ ለሚመጣዉ ጉዳት ተጠያቂ ነው።
3.24 አንድ አባል የመጀመሪያ እጣ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ብሩን ተመላሽ መጠየቅ ይችላል፡፡
3.25 አባሉ እጣ ውሰጥ መግባት የሚችለው የመጀመሪያውን መዋጮ ሙሉ ለሙሉ ከከፈለ ብቻ ይሆናል በተጨማሪም የመጀመሪያው እጣ ከወጣ በኋላ በየ ሶስት ወሩ ለሚከናወነው እጣ ማውጣት ቢያንስ ከ አንድ ወር ያልበለጠ የመዋጮ እዳ ከሌለበት ብቻ ይሆናል'።
3.26 አንቅጽ 3.25 እንደተጠበቀ ሆኖ አባሉ እጣ ዉስጥ የሚገባዉ በየሶስት ወሩ ለድጎማ ቁጠባው አንቀጽ 4.1 በፊደል ሰ የገባዉን ግዴታ ከተወጣ ብቻ ይሆናል።
3.27 አባሉ የመኪናውን ወጪ መቶ በመቶ ከፍዬ ልውሰድ ካለ ለድርጅቱ በአንቀፅ 4 ያሉትን ሁሉንም የሚቀርበትን ወርሃዊና አመታዊ አገልግሎት ክፍያ ፣ ኮሚሽን ጠቅልሎ ከፍሎ በተጨማሪም ሌሎች አባላት ለወደፊት የመኪና ዋጋ ቢጨምርባቸዉ ጭማሪዉን ብር ሊጨምር የዉዴታ ግዴታ ዉል ገብቶ መውሰድ ይችላል፡፡
3.28 አንድ አባል እቁቡን ሲከፍል ቆይቶ ከዚህ አለም በሞት ቢለይ በሟች ስም የተመዘገበ እቁብ ገንዘብ ለመቀበል የሚችል በፍ/ቤት ወራሽነቱን አረጋግጦ ያቀረበ ወራሽ ብቻ ነዉ፡፡ ወራሹ ሟች የሚፈለግበት የዋስትና እዳ ወይም ወደ ኋላ ያልተከፈለ እዳ ካለ የመክፈል በተጨማሪም አባሉ ለድርጅቱ ለመክፈል የተስማማቸዉን ክፍያዎችን በሙሉ የመክፈል ግዴታ አለበት።
3.29 አንድ አባል ከአባላት ውስጥ ዋስ ማግኘት ሳይችል ቀርቶ ከአባላት ውጪ በቂ ንብረት ያለው ዋስ ካቀረበ እና የሚጠበቅበትን ግዴታ ከተወጣ በተጨማሪ ዋሱ ኦርጂናሉን ማስረጃ አቅርቦ በዋስትና በማስያዝ ከፈረመ ይስተናገዳል፡፡ነገር ግን አንድ አባል እጣ ደርሶት ዋስ ለማቅረብ ካልቻለ ንብረቱ በድርጅቱ ጥበቃ ስር ይቆያል ወይም ለሌላ አባል በእጣ ይተላልፋል እንጂ ያለ ዋስ ይሰጠኝ ብሎ መጠየቅም ወይም እስከ ዛሬ ያስቀመጥኩት ገንዘብ ይመለስልኝ ማለት አይችልም፡፡
3.30 አባሉ ከደርጅቱ ከመኪና ወጪ ማንኛውም አይነት ጥቅሞች መጠየቅ አይችልም፡፡
አንቀጽ 4
የክፍያ አፈጻጸም
4.1 አባሉ የሚከተሉትን ክፍያዎች በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ወይም በአባሉ ስም በአትራፊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃ/የተ/ህ/ስ/ማ በተከፈተ ዝግ የሂሳብ ቁጥር እና በድርጅቱ ስም በተከፈተ ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ ዉስጥ ገቢ ያደርጋል፣
ሀ/ ይህ ዉል እንደ ተፈረመ ቅድመ መመዝገቢያ አገልግሎት ክፍያ ብር 19,000 (አስራ ዘጠኝ ሺህ ) በድርጅቱ ስም በተከፈተ ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ ገቢ ያደርጋል።
ለ/ ለራሱ ቁጠባ 60,000 (ስልሳ ሺህ ) ብር በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ያደርጋል።
ሐ/ አባሉ የመጀመሪያዉ እጣ ከወጣበት ወር ጀምሮ በየወሩ 20,000 (ሃያ ሺህ ብር) ለተቀማጭ በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና 2000 (ሁለት ሺህ ብር) ለአገልግሎት ክፍያ በድርጅቱ ስም በተከፈተ ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ያደርጋል፡፡
መ/ አባሉ የመኪና እጣ በደረሰው ጊዜ የመኪናዉን 15 በመቶ ቅድመ ክፍያ ብር በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ያደርጋል፡፡
ሠ/ አባሉ እጣዉ ከደረሰዉ በኋላ በየወሩ የእዳዉን ተመላሽ 10% (አስር በመቶ ) የአገልግሎት ክፍያ በድርጅቱ ስም በተከፈተ ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ እና 40,000 (አርባ ሺህ ብር ) የእዳ ተመላሽ በዝግ የሂሳብ ቁጥር ገቢ ያደርጋል፤ እዳዉን ከፍሎ እስኪጨርስም የአገልግሎት ክፍያ ያለሟቋረጥ ይከፍላል በተጨማሪም አባሉ በየወሩ እየከፈለ እዳዉን እንዲጨርስ ከሚሰጠዉ ዓመት በፊት እዳዉን ከፍሎ ቢጨርስም አጠቃላይ ይከፍልባቸዉ የነበሩት ወራቶች ተሰልተዉ አገልግሎት ክፍያ ጠቅልሎ ለመክፈል ተስማምቷል።
ረ/ አንቀጽ 4.1 .ሠ እንደተጠበቀ ሆኖ አባሉ የመኪና እጣ ከደረሰው በኋላ ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያው ላይ እና የራሱ ተመላሽ እዳ ላይ ድርጅቱ ማስተካከያ ካደረገ በተስተካከለዉ ክፍያ መሰረት ክፍያውን ለመፈጸም ተስማምቷል።
ሰ/ አባሉ በየሶስት ወሩ እጣ በሚወጣበት ጊዜ የድጎማ መዋጮ ቁጠባ 60,000 (ስልሳ ሺህ ብር) በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ያደርጋል።
ሸ/ አባሉ የመኪና እጣ በደረሰዉ ጊዜ በአንድ ጊዜ የሚከፈል ለድርጅቱ የአገልግሎት ክፍያ የመኪናዉን 10 በመቶ ብር በድርጅቱ ስም በተከፈተ ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ ገቢ ያደርጋል ይህ ክፍያ ከሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ጋር የማይታሰብ ነዉ ። አባሉ ይህን ክፍያ በ አንድ ጊዜ መክፈል ካልቻለ ድርጅቱ በወራት እንዲከፍል ያመቻችለታል፡፡
ቀ/ አባሉ ከላይ የተዘረዘሩትን በድርጅቱ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር የሚፈፀሙ ክፍያዎችን በአባሉ ስም በአትራፊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃ/የተ/ህ/ስ/ማ በተከፈተ ዝግ የሂሳብ ቁጥር የመክፈል አማራጭ አለው፡፡ ስለሆነም መጀመሪያ ላይ በመረጠው አማራጭ እስከ መጨረሻው የመቀጠል ግዴታ አለበት፡፡
4.2 አባሉ በዉሉ መሰረት የወር መዋጮዎችን እና ክፍያዎችን ቀድሞ ከከፈለ እና ድርጅቱ የዋጋ ግሽበት ምክንያት የክፍያ ማስተካከያ ካደረገ ቀሪዉን ክፍያ አሟልቶ ይከፍላል።
4.3 ማንም አባል እጣ ደርሶት ከወሰደ በኃላ ክፍያዉን ቢያቋርጥ ፤
ሀ/ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ወር በሚከፍለዉ አጠቃላይ ክፍያ ላይ 10% (አስር በመቶ) ተቀጥቶ ይከፍላል ፡፡
ለ/ በሶስተኛ ወር በሚከፍለዉ አጠቃላይ ክፍያ ላይ 10% (አስር በመቶ) መቀጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ ከሚከተሉት በአንዱ አማራጭ በስልክ ወይም በሶሻል ሚዲያ ቴክስት ፣ በኢሜል ፣ በአካል ፣ በአድራሻዉ በደብዳቤ ወይም በድርጅቱ ቦርድ ላይ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ያለበትን ገንዘብ አንድ ጊዜ ቀርቦ እንዲከፍል ከነዋሶቹ ጭምር ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል፡፡ በደረሰው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰረት በሰባት ቀናት ዉስጥ ቀርቦ ካልከፈለ በድርጅቱ የህግ ባለሙያ እና ጠበቃ ወይም ነገረፈጅ አማካኝነት በፍ/ቤት ከነዋሶቹ ክስ ይመሰረትበታል፡፡
ሐ/ አባሉ ክስ በሚመሰረትበት ጊዜ ንብረቱን የገዛዉ በሌሎች አባላት ገንዘብ እንደመሆኑ መጠን የአባላቱን ገንዘብ ለመጠበቅ ሲባል ድርጅቱ ባዘጋጀለት ቦታ ላይ መኪናዉን ከስራ ዉጪ አድርጎ ለማስቀመጥ የዉዴታ ግዴታ ገብቷል በተጨማሪም በሚቆምበት ጊዜ ለጥበቃ እና ለማሳደሪያ ድርጅቱ የሚጠይቀዉን ክፍያ ለመክፈል ተስማምቷል ።
መ/ ክስ ከተመሰረተበት በኋላ የዳኝነት የጠበቃ አበልና ልዩ ልዩ ወጪዎች ጋር አጠቃሎ የሚከፈል ይሆናል፡፡
4.4 እጣ ሳይደርሳቸው ክፍያ ስለሚያቋርጡ አባሎች
ሀ/ ክፍያዉን ባቋረጠ በመጀመሪያዉ ወር በሚከፍለዉ መዋጮ ላይ 1% (አንድ በመቶ) መቀጫ ይከፍላል ዕጣ ቢወጣለት ተመላሽ ይሆናል ።
ለ/ በድጋሚ ክፍያዉን ባቋረጠ በሁለተኛው ወር ክፍያውን ባይከፍል በሚከፍለዉ መዋጮ ላይ ብር 2 %( ሁለት በመቶ) ይቀጣል እጣው ተመላሽ እንደሆነ ይቆያል፡፡
ሐ/ በሶስተኛ ወር ክፍያውን ቢያቋርጥ በሚከፍለዉ መዋጮ ላይ ብር 3 % (ሶስት በመቶ ) መቀጫ ከፍሎ እጣውም ሳይሰራ የዋስትና እዳ ቢኖርበት ገንዘብ ይቆረጣል ፤ በየወሩ ባለመክፈሉ የሌሎች እቁብተኞችን ድርሻ በማስተጓገሉ እስከ እቁቡ ማብቂያ በሚከፍለዉ ወራዊ መዋጮ ላይ 3% (ሶስት በመቶ ) እየተቀጣ ይሄድ እና በእቁቡ መጨረሻ ላይ ቀሪውን ገንዘብ ታስቦ ይወስዳል፡፡
4.5 ድርጅቱ በአባሉ በኩል የሚከፈሉ ክፍያዎችን ከድርጅቱ አካዉንት ዉጪ በጥሬ ገንዘብም ሆነ በሌሎች አማራጮች ክፍያ አይቀበልም ።
አንቀጽ 5
የዉል ዘመን ፣ ተፈጻሚነት ፣ ውል የሚቋረጡባቸዉ ምክንያቶች እና ዉጤቶቹ
5.1 ይህ ዉል ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ለ10 (አስር) ዓመት ጸንቶ ይቆያል ። ዉሉ በሚከተሉት ሁኔታዎች ሊቋረጥ ይችላል።
ሀ/ በሁለቱም ወገኖች የጽሁፍ ስምምነት፣
ለ/ የዉል ዘመኑ ሲያልቅ፣
ሐ/ አስቀድሞ ያልታወቀ እና ያልተገመተ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ሲያገጥም፣
መ/ በዉሉ መሰረት በማናቸዉም ምክንያት የዉሉ ሁኔታዎች በአግባቡ መፈፀም ሳይችሉ ሲቀር
5.2 ይህ ዉል በኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 መሰረት በሕግ ፊት የፀና ነዉ ። አባሉ ዉሉን በትክክል በማንበብ በዉሉ ለመገዛት ፈቃደኛ ከሆነ “ደንቦችና እና ሁኔታዎችን አንብቤ ተስማምቻለዉ” የሚለዉን የሚጫን ሲሆን ይህን ሲያደርጉ የዚህን ዉል ደንብና ሁኔታዎች በመቀበል አባል ይሆናሉ።
5.3 ይህ ውል በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ለሚፈጠር አለመግባባት በዋና ህግነት ያገለግላል፡፡
5.4 በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ያለመስማማት በሚፈጠርበት ጊዜ ወደ ህግ ከመሄዳቸዉ በፊት ጉዳያቸዉ በሽማግልና ይታያል፡፡
አንቀጽ 6
የዉል አካል የሆኑ ሰነዶች
6.1 የሚከተሉት ሰነዶች የዚህ ዉል አካል ይሆናሉ
ሀ/ አባሉ የመኪና እጣ ሲደርሰዉ የሚዋዋለዉ ዉል ፣
ለ/ በዚህ ዉል መሰረት አባሉ ለድርጅቱ የሰጠዉ ዉክልና ስልጣን እና የመኪና ሰነድ ፣
ሐ/ ሌሎች አባሉን አስመልክቶ የሚወጡ በድርጅቱ የተላለፉ መመሪያዎችና በድርጅቱ ለአባሉ የተጻፉ ደብዳቤዎች ናቸዉ ።
6.2 በዚህ ውል እና ከላይ በተገለጹት ሰነዶች መካከል ልዩነት ቢፈጠር በዚህ ዉል የተገለፀዉ ሀሳብ ገዢ ይሆናል
አንቀጽ 7
ጠቅላላ ሁኔታዎች
7.1 ሁለቱም ወገኖች ለህብረተሰቡ መኪና ማግኘት የሚያስችለዉን ፕሮግራም ያስተዋውቃሉ።
7.2 ድርጅቱም ሆነ አባሉ የሚፈለግባቸዉን የየራሳቸዉን ታክስና መንግስታዊ ግዴታዎቻቸዉን ይወጣሉ::
7.3 ይህ ዉል የሚታየዉ የሚፈጸመዉ እና የሚተረጎመዉ አግባብነት ባላቸዉ የኢትዮጵያ ህግ ድንጋጌዎች መሰረት ያሆናል፡፡
7.4 ድርጅቱ የዚህን ዉል ደንብና ሁኔታዎች ለአባላት በማሳወቅ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ሊያሻሽል ይችላል።
7.5 በዚህ ዉል ዉስጥ የማንኛዉም ድንጋጌ ወይም ሁኔታ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ መከልከል ወይም ዋጋ ማጣት ወይም ሕገ-ወጥ መሆን ( የዉሉን ተፈጻሚነት ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ካልሆነ በቀር ) በዉሉ ዉስጥ ያሉ ሌሎች ድንጋጌዎችን ወይም ሁኔታዎችን ዋጋ አያሳጣም ተፈጻሚነታቸዉን አያስቀርም።
7.6 በዚህ ዉል ዉስጥ በወንድ ጾታ የተገለጸዉ አገላለጽ በተመሳሳይ መልኩ ለሴትም ጾታ ያገለግላል ። በተጨማሪ በብዙ ቁጥር የተገለጹ ጾታዎች አባሉን ይገልጻሉ።